የ”ላንዳፍታ” ታሪክ – History of “LANDAFTA”

ኢትዮጵያን ላንዳፍታ

የፍቅር፤ የሰላምና የአንድነት ሚዲያ ኔትወርክ

በፍቅር፤ በሰላምና  በአንድነት  ተከባብሮ ለመኖር፤ መደማመጥ! መቻቻል!

በአገራችን ኢትዮጵያ ወገኖቻችን በአሁኑ ጊዜ እያጣጣሙት ያሉትን የፍቅር፤ የሰላምና የአንድነት  ክስተቶች በውጭ አገር ያለው፤ ተከፋፍሎና ተለያይቶ የነበረው ወገናችን የዚህ በጎ ተግባር ተቋዳሽ ሆኖ አንድነቱን እንዲያጠናክር ትክክለኛ መረጃ ያላቸውን ዜናዎችና ሐተታዎች ማቅረብ፤ ወገንን የሚያኮሩ እየተከናወኑ ያሉ በጎ ተግባራትን ማሳወቅ፤  አዝማሚያችው የማያምር አፍራሽ የሆኑና ለአንድነቱ ጸር የሆኑ እንቅስቃሴዎችን ማጋለጥና በሁለቱም ወገን ያሉትን ማቅረብና ኅብረተሰቡ እውነትኛ ግንዛቤ እንዲኖረው ማድረግ የዝግጅት ክፍላችን ዓይነተኛ ተግባር ይሆናል።

ኢትዮጵያን ላንዳፍታ የተሰኘው ይህ የሚዲያ ኔት ወርክ ፕሮግራሞቹን በዩቲብና በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች የሚያቀርብ ይሆናል። ዓላማውም ቀደም ሲል የላንዳፍታ መጽሔት ያራምድ የነብረውን መርሆ፤ በፍቅር በሰላምና በአንድነት ተከባብሮ ለመኖር መደማመጥ መቻቻል መሠረት ያደረገና በለውጡ ሳቢያ የመጡትን ድሎችና በተለይም በሕዝቦቻችን መካክል እንዲፈጠር የተወጠነው በፍቅር ላይ የተመሠረተ ሰላምና አንድነት ተጠናክሮ ቅራኔዎች እንዲላሉ ለማገዝ ትክክለኛ መረጃ ዎችን ለማቅርብና በሕዝቦች መካከል ዴሞክራሲን መሠርት ያደርጉ ሥርዓት ያላቸው ውይይቶች የሚካሄድባችውን መድርኮች ለመፍጠር ነው።

አጀማመራችን

እስቲ በጥቂቱ ስለ አነሳሳችን ማለትም ጥቂት ጀባ እንበላችሁ። በእኛ አቆጣጠር በ1983  እኤአ በ1991 በአገራቸን በመጣው የፖለቲካ ለውጥና የደርግ መውደቅ ጋር ተያይዞ በመጣው አዲስ ዘር ተኮር ፖለቲካ ምክንያት በውጭ አገር በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን መካከል እየተፈጠረ የሄደውን መለያየት በመመልከት “በፍቅር በሰላምና በአንድነት ተከባብሮ ለመኖር መደማመጥ! መቻቻል!” በሚል ዓላማ ተነሳስተን በአማርኛ ብቻ ስትታተም የነበረችው “ላንዳፍታ” የተስኘችው መጽሔት ለዛሬዋ ኢትዮጵያው ላንዳፍታ መሠረት ናት።

“ኢትዮጵያን ሪቪው” የተሰኘችው መጽሔት ካሊፎርኒያ በመስከረም 1983 (September  1991) በእንግሊዝኛ ቋንቋ  ስትጀምር “ላንዳፍታ” ደግሞ ከስድስት ወራት በኋላ በአማርኛ ቋንቋ  ቺካጎ ከተማ በየካቲት 1983  (February 1991) ጀመረች።

በዚያን ወቅት የግዕዝ ፊደላትን የሚጠቀም የኮምፒውተር ፕሮግራም በጣም ብርቅዬ ነበረ። ካሊፎርኒያ ፍስሐ አጥላው ባዘጋጀው   የተሰኘው ፕሮግራም የመጀመሪያውን ሁለት እትሞች ከዚያ በኋላ ያሉት እትሞች በሙሉ የታትሙት ዶ/ር አበራ ሞላ ከዴንቭር ኮሎራዶ በፈጠሩዋቸው ሞዴት፤ ግዕዝ ኤዲት ወዘተ ተብለው በሚጠሩ የሶፍት ዌር ፕሮግራሞች ነበር። በሺካጎ አካባቢ ብቻ የተሰራጨችው የመጀመሪያዋ እትም የተባዛችው ኪንኮስ ተብሎ በሚጠራው የኮፒ መደብር በኮፒ ማሽን ነበር። በጣም ውድ ነበረ።

ቀጠል አድርገን ደግሞ በመጽሔቷ ይቀርቡ የነበሩትን የተለያዩ አምዶችን በአጭሩ እናስቃኛችሁ።

ሰላምታ ከወደ አገር ቤት፤ ሰላምታ ከወደ አሜሪካ

በብዕር ስም ወርቃየሁ ከአገር ቤት፤ ገብርዬና ይግለጡ ደግሞ ከዚሁ ከአሜሪካ ይለዋወጡ የነበሩት ደብዳቤዎች በአንባቢያን ዘንድ ከፍተኛ ተነባቢነትና ተወዳጅነት ነበራቸው።ወርቃየሁ ከአገር ቤት በኑሮ ላይ የሚታዩትን ችግሮች፤ ደርግን ጥሎ መንግሥት በሆነው ኢህአዴግ የሚደረገውን ጫናና እመቃ፤ ገብርዬ ደግሞ ከዚሁ ከአሜሪካ  በውጭ አገር ደግሞ በኢትዮጵያውያን የሚደረገውን ትግል፤ በተለይም እርስ በርስ የሚደረገውን መነቋቆር በበሰለና ምሁራዊ ብዕሩ የተለዋወጧቸው ደብዳቤዎች ትልቅ ትውስታ አላቸው።

አዳምና ሄዋን፤

አዳምና ሔዋን በሚል አምድ በወንድና በሴት ግንኙነት መካከል ሊኖሩ ስለሚገቡ ሥነሥርዓቶች፤ አንዱ ወይም አንዷ ሌላዋን ወይም ሌላውን ለማወቅና ለማግባባት በሎም የፍቅር ግንኙነት ለመፍጠር በሚደረጉ እንቅስቃሴ ወቅት መደረግ የሚገባችውና የማይገባችውን ንግግሮችና አቀራረቦች በመጠቆም 

የአንባብያን ደብዳቤዎች አምድ

በተጨማሪም አንባብያን የላኩዋቸው ደብዳቤዎች በሥርዓቱ ተስተናግደዋል።

ቃለ መጠይቅ

የተለያዩ የፓለቲካ ድርጅት መሪዎችን፤ ፖለቲካል አክቲቪስቶችን፤ ምሁራንን የሃይማኖት መሪዎችን አርቲስቶችን የኮሚኒቲ ሃላፊዎችን ቃለ መጠይቅ አድርገናል።

እንዲህ ሆነ

“እንዲህ ሆነ!” በሚል አምድ የተለያዩ የአገር ቤትና በውጭ አገር ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን የተመለከቱ ዜናዎችን ታቀርብ ነበር።

ኑሮ በአሜሪካ፤

ኑሮ በአሜሪካ በተሰኘው አምዳችን ደግሞ በስደትና በተለያዩ ምክንያቶች አገራቸውን ለቀው ወደ አሜሪካ የመጡ ወገኖቻችን ሊገጥማችው የሚችለውን የኑሮ ችግሮችን በመጠቆም መፍትሔ ሊሆኑ ይችላሉ ተብለው የሚገመቱ ሃሳቦችን አቅርበናል። በተለይም በባህል ግጭት ምክንያት ሊፈጠሩ የሚችሉ ችግሮችን መቋቋሚያ ይሆናሉ ያልናችውን ሃሳቦች ጠቁመናል።

ስነጽሁፎች

በገጠመኝ ላይ ተመስርተው የቀረቡት ተከታታይና አጫጭር ልብ ወለድ ታሪኮች

ተከታታይ ልብ ወለድ ታሪኮች

  • “የዴብራ ጦስ”
  • “ዕጣዬ”
  • “አላለልኝ ይሆን?”
  • “እልፍ ሲሉ እልፍ ሊገኝ”  የተሰኙት ከብዙዎቹ ጥቂቶቹ ናቸው።

አጫጭር  ልብወለዶች

  • “ውበት”
  • “የኮለምበስ ጉዞ”  የተሰኙት ከብዙዎቹ ጥቂቶቹ ናቸው።

በብዙ አንባብያን ዘንድ ተደናቂነትን ያተረፉ ቀጥለው የተዘረዘሩት ከአንባቢያን የተላኩና በዝግጅት ክፍላችን የተቀነባበሩ የስነ ጽሁፍ ክፍሎችም  በፍጹም የሚረሱ አይደለም።የአማርኛ ፈሊጦች፤

  • ተረትና ምሳሌዎች፤
  • ግጥሞች፤

ዕውቀትና ምክር አዘል የሆኑ በሳል መጣጥፎች፤

የአገር ቤትን ጉዳይ በተለይም የፖለቲካ፤ የማህበራዊና የኤኮኖሚ ጉዳዮችን በተመለከተ የተለያዩ ግለሰቦች የጻፉትን መጣጥፎችን፤

የስንጠረዥና አዕምሮን ማጎልምሻ ጨዋታዎች